Amharic(i)
1 ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 2 አሕዛብ ሳላችሁ በማናቸውም ጊዜ እንደምትመሩ ድምፅ ወደሌላቸው ወደ ጣዖታት እንደ ተወሰዳችሁ ታውቃላችሁ። 3 ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር። ኢየሱስ የተረገመ ነው የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር። ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። 4 የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ 5 አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ 6 አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 7 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። 8 ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ 9 ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ 10 ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ 11 ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። 12 አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 13 አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። 14 አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። 15 እግር። እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? 16 ጆሮም። እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 17 አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 18 አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። 19 ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? 20 ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው። 21 ዓይን እጅን። አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን። አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። 22 ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ 23 ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 24 ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። 26 አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 27 እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 28 እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል። 29 ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? 30 ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን? 31 ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።13 1 በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። 2 ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3 ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 4 ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ 5 የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ 6 ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ 7 ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 8 ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። 9 ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ 10 ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። 11 ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። 12 ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። 13 እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።14 1 ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ። 2 በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፥ በመንፈስ ግን ምሥጢርን ይናገራል፤ 3 ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። 4 በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበሩን ያንጻል። 5 ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፥ ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጐም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል። 6 አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ? 7 ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል? 8 ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9 እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና። 10 በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤ 11 እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። 12 እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ። 13 ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ። 14 በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። 15 እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። 16 እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? 17 አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም። 18 ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 19 ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ። 20 ወንድሞች ሆይ፥ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ። 21 ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎችና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ፥ እንዲህም ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ ተብሎ በሕግ ተጽፎአል። 22 እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። 23 እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ። አብደዋል አይሉምን? 24 ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ 25 በልቡም የተሰወረ ይገለጣል እንዲሁም። እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። 26 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 27 በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤ 28 የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። 29 ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 30 በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል። 31 ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ። 32 የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፤ 33 እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው። 34 ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና። 35 ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ። 36 ምን ነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን? 37 ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ 38 ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ። 39 ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ 40 ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።