Acts 17:1-8

Amharic(i) 1 በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። 2 ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ 3 ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ። ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ይል ነበር። 4 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። 5 አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤ 6 ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው። ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ 7 እነዚህም ሁሉ። ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ ብለው ጮኹ። 8 ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፥