Acts 2:23-32

Amharic(i) 23 እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። 24 እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። 25 ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። 26 ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ 27 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። 28 የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ። 29 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። 30 ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ 31 ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። 32 ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤