Amharic(i)
24 መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። 25 አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። 26 በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። 27 ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። 28 እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ 29 ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። 30 የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። 31 በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። 32 የሎጥን ሚስት አስቡአት። 33 ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። 34 እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። 35 ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። 36 ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። 37 መልሰውም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም። ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው።