Amharic(i)
7 ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? 8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና። 9 አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 10 ሕዝቡም። እንግዲህ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። 11 መልሶም። ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ ይል ነበር። 12 ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው። መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት። 13 ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው። 14 ጭፍሮችም ደግሞ። እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም። በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው።