Amharic(i)
3 ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥ 4 ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። 5 ፈሪሳውያንም ጻፎችም። ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። 6 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ 7 የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። 8 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። 9 እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። 10 ሙሴ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና። 11 እናንተ ግን ትላላችሁ። ሰው አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥ 12 ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ 13 ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።