Revelation 13:11-17

Amharic(i) 11 ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር። 12 በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል። 13 እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል። 14 በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል። 15 የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። 16 ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ 17 የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ።