Romans 12:1-13:14

Amharic(i) 1 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። 2 የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። 3 እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። 4 በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ 5 እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። 6 እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ 7 አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ 8 የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። 9 ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ 10 በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ 11 ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ 12 በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ 13 ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። 14 የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። 15 ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። 16 እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። 17 ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። 18 ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። 19 ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። 20 ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። 21 ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።13 1 ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። 2 ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። 3 ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ 4 ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። 5 ስለዚህ ስለ ቍጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። 6 ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። 7 ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። 8 እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። 9 አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። 10 ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። 11 ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። 12 ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። 13 በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ 14 ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።