Amharic(i)
44 ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። 45 እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? 46 ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ 47 እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48 ያ ክፉ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ 49 ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ 50 የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ 51 ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።25 1 በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። 2 ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። 3 ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ 4 ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። 5 ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። 6 እኩል ሌሊትም ሲሆን። እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። 7 በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። 8 ሰነፎቹም ልባሞቹን። መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። 9 ልባሞቹ ግን መልሰው። ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። 10 ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። 11 በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። 12 እርሱ ግን መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። 13 ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።