Amharic(i)
1 አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። 2 ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው። 3 ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ 4 ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። 5 ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። 6 እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። 7 ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።