Matthew 4:1-10

Amharic(i) 1 ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥ 2 አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። 3 ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። 4 እርሱም መልሶ። ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። 5 ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ። 6 መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። 7 ኢየሱስም። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። 8 ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። 9 ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። 10 ያን ጊዜ ኢየሱስ። ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።